ዘመቻ ቆሞ መሄድ
Amharic
Mahelet Lisanwork
Unable to view? Click here.
በድሮ ዘመን ሰዎች እንደ ሌሎች እንስሳቶች ሁሉ በአራት እግራቸው ማለትም በእጅ እና በእግራቸው ነበር የሚራመዱት ፡፡ ሰዎች ከጥንቸል፣ ከነብር እና ከአውራሪስ ሳይቀር ፈጣኖች ነበሩ፡፡ የትከሻ እና የሽንጥ፣ የክርን እና የጉልበት፣ የቁርጭምጭሚት እና የእጅ መጋጠሚያ እንዲሁም ጥፍር እና አምስት ጣቶች ያሉዋቸው እጆች እና እግሮች መገጣጠሚያቸው ትይዩ ስለነበር ከየትኛውም የሰውነት ክፍል ይልቅ ቅርርብ ነበራቸው፡፡ ከአውራ ጣት ጀምሮ እስከ ትንሹ ጣት ተመሳሳይ የነበሩት የእጅ መዳፍ እና እግሮች አንድ አይነት አቀማመጥ ነበራቸው፡፡ በዛ ዘመን የእጅ አውራ ጣት እንደ እግር አውራ ጣት ከሌሎቹ ጣቶች ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ስለዚህም እጅ እና እግር እንደ ትልቅ ዘመድ ይተያዩ ነበር፡፡
ሱቅ ይሁን ገበያ፣ ዛፍ መውጣት ይሁን ተራራ፤ ሰውነት መሄድ ወደ ፈለገበት ሁሉ ተጋግዘው ይወስዱት ነበር፡፡ ውሃ ውስጥ እንኳን ሰውነት እንዲንሳፈፍ፣ እንዲዋኝ እና እንዲጠልቅ በህብረት ይረዱት ነበር፡፡ ግንኙነታቸው በበዲሞክራሲ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ነበረ። በተጨማሪም የሌሎች የሰውነት አካላትን ችሎታዎች ማለትም ከአንደበት ድምፅን፣ከጆሮ መስማትን፣ ከአፍንጫ ማሽተትን እንዲሁም ከአይን ማይትን ይዋሱ ነበር፡፡
በጣም መዋሃዳቸው እና መግባባታቸው ውሎ ሲያድር በሌሎች የሰውነት አካላት ዘንድ ቅናት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ቅናቱም እግር እና እጅ እንደሚያንቀሳቅሷቸው አስረስቶ እነሱን ለማጋጨት እንዲያሴሩ አደረጋቸው፡፡
ምላስም ከአዕምሮ የተቀበለችውን ሃሳብ በፍጥነት በመተግበር ከእግር እና ከእጅ ማናቸው ሀይለኛ ናቸው ብላ ጮኸች በመላ ሰውነትም አስተጋባች፡፡ በዚህም የተነሳ የልብ ወዳጆች የነበሩት ስለ ችሎታቸውም ሆነ ስለማንነታቸው አስበው የማያውቁት እጅ እና እግር ከአንደበት ድምፅ ተውሰው ለሰውነት የበለጠ የማስፈልገው እኔ ነኝ እኔ ነኝ ማለት ጀመሩ፡፡ ወዲያውኑም ማነው ለግላጋ የሚለው ጥያቄ ተነሳ፡፡ እጅም ስለ አለንጋ ጣቶቹ ጉራ መንፋቱን ጀመረ በዛውም ስለ እግር ጣቶች ውፍረት እና እጥረት ሀሳብ መስጠቱን ተያያዘው፡፡ ማን ከማን ያንሳል የእግር ጣቶችም አለንጋ የእጅ ጣቶችን ረሃብተኞች እያለ ተቸ፡፡ ለቀናት የዘለቀው ይህ ጭቅጭቅ አብሮ የመስራት ችሎታቸውን አዳከመው፡፡ በመጨረሻም ይህ የሃያልነት ጥያቄ በሌሎች የሰውነት አካላት ዳኝነት እንዲፈታ ተወሰነ፡፡
ምላስ በሁለቱ መካከል ውድድር ይካሄድ የሚል ሃሳብ አቅርባ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት አገኘች፡፡ ሆኖም ውድድሩ ምን ይሁን የሚለው የሁሉም ጥያቄ ሆነ፡፡ አንዳንዶች በእጅ እና በእግር መካከል ትግል ይደረግ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ የሰይፍ ጨዋታ ፣ቅልልቦሽ፣ ግልብያ እንዲሁም እንደ ቼስ ያሉ ጨዋታዎችን አሉ፡፡ ሁሉም ጨዋታዎች ግን ለአንዱ አካል ተገቢ ባለመሆኑ ወይንም ከባድ በመሆኑ ውድቅ ተደረገ፡፡ እንደተለመደው ምላስ ከአይምሮ ሃሳብ በመዋስ የመፍትሄ ሃሳብ አመጣች፡፡ ተፎካካሪዎቹ እራሳቸው አንዱ ለሌላኛው ፈተናውን ያዘጋጅ አለች፡፡ እጅ እና እግርም በሃሳቡ ተስማሙ፡፡
ውድድሩ በጫካ ውስጥ ከወንዝ አቅራቢያ በሚገኝ የተመነጠረ ሜዳ ላይ ተካሄደ፡፡ ከሰውነት አካላት ውስጥ ሁለቱ በውግያ ላይ በመሆናቸው የተቀሩት አካላት በሙሉ ሊያጋጥም የሚችል የትኛውም አይነት አደጋንም ሆነ ያልታሰቡ ነገሮችን በንቃት እየተከታተሉ ነው፡፡ አይኖች ከየትኛውም ርቀት ሊመጣ የሚችልን አደጋ አማትረው ያያሉ፤ ጆሮዎች ከየትኛውም ርቀት የምትመጣ ድምፅን ለመስማት እራሳቸውን አጠሩ፡፡ አፍንጫም ከአይን እይታና ከጆሮ ያመለጡ አደጋዎችን በሚገባ ለማሽተት እራሱን አፀዳ፡፡ ምላስም አደጋን ጮሆ ለማሳበቅ ተዘጋጅቷል፡፡
የውድድሩ ዜና በጫካው፣ በአየር እና በውሃ አካላት በአራቱም ማዕዘን ተናፈሰ፡፡ የውድድሩ እለት በአራት እግራቸው የሚንቀሳቀሱ እንስሳቶች በስፍራው ቀድመው ተገኙ፡፡ ትላልቆቹ እንስሳቶች ደግሞ በሰላም መምጣታቸውን ለመግለፅ አረንጓዴ ቅጠሎችን ይዘው ነበር፡፡ የነብር፣ የአቦ ሸማኔ፣ የአውራሪስ፣ የአንበሳ፣ የጅብ ፣የነብር፣የቀጭኔው፣የዝሆኑ፣ የግመሉ፣ ባለ ረጅም ቀንድ ከብቶች ፣ የጎሹ፣የድኩላ፣ የአጋዘኑ፣የሜዳ ፍየሎች፣ የጥንቸሉ፣ የፍልፈል እና የአይጡ ስብስብ የሚያምር ድምቀት ነበረው፡፡ በውሃ ውስጥ የሚኖሩት ጉማሬ፣ አሳ፣ እና አዞም ግማሽ አካለቸውን ውሃ ውስጥ ግማሹን ደረቅ መሬት ላይ በማድረግ ፕሮግራሙን ታድመዋል፡፡ ባለ ሁለት እግሮቹ ሰጎን፣ጅግራ እና ፒኮክ በደስታ ክንፋቸውን አራገቡ፡፡ ወፎች ዘመሩ፣ ፌንጣም በደስታ ዘለለች፣ ሸረሪት፣ መቶ እግር፣ ሺ እግር እና ሌሎች ትላትሎች በዛፎች እና በመሬት ላይ ተሳቡ፡፡ እስስት በዝግታ ጊዜዋን ወስዳ ስትጓዝ እንሽላሊት ደግሞ አንዴ እንኳን ሳታርፍ እላይ ታች ትል ነበር፡፡ ጦጢት እና ዝንጀሮዎች ከዛፍ ዛፍ ዘለሉ፡፡ ዛፎች እና ጫካው እንኳን በዝግታ ከ አንዱ ወደ ሌላ አቅጣጫ ነፈሱ፣ እጅ ነሱ ከዛም ፀጥ አሉ፡፡
አፍም የውድድሩን መጀመር በዝማሬ አበሰረች፡፡
ተፈጥሮ እናታችን፣
አንቺ ነሽ ምንጫችን፣
ባንቺ ለመደሰት ነው መሰብሰባችን፣
ባንቺ ለመደሰት ነው መሰብሰባችን፣
ባንቺ ለመደሰት ነው መሰብሰባችን፡፡
እጅ እና እግር የውድድሩ ውጤት ምንም ይሁን ምን በፀጋ ለመቀበል ቃል ገቡ፤ቁጣ ፣ጥላቻም ሆነ ማስፈራራት ወደ ኋላ መመለሰም ሆነ ማቋረጥ እንደሌለ ተስማሙ፡፡
እጅ የመጀመርያውን የግጥሚያ ጥሪ ለእግር አቀረበች፡፡ ግጥሚያው መሬት ላይ ያለን እንጨት አንስቶ መወርውር ሲሆን ግራ፣ ቀኝ ወይንም ሁለቱንም እግሮች መጠቀም ይቻላል፡፡ ሁለቱ እግሮች በየትኛውም ሰአት የመመካከር እና የትኛውንም ጣት በተናጠልም ሆነ በህብረት ለውድድሩ አመቺ በሆነ መንገድ የመጠቀም ነፃነት አላቸው፡፡ እግሮች እንጨቱን በትክክል አንስቶ የመወርወሩ ስራ ዳገት የመግፋት ያህል አዳገታቸው፤ በመግፋት፣ በማገላበጥ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች ለማንሳት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም መወርወሩም አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ትንሽ ርቀት ብቻ አንቀሳቀሱት፡፡ ይህንን ያየችው እጅ ከአፍ ድምፅ ተውሳ እስኪበቃት አሽካካች ቀጠል አድርጋም የቁንጅና ውድድር ላይ ያለች ይመስል ለግላጋ ውበቷን ለማሳየት ተንጎራደደች፤ ምን ይሄ ብቻ ዕንጨቱን በተለያየ መንገድ በማንሳት ወደ ጫካው አርቃ በመወርወር ታዳሚውን አስደመመች፡፡ እግሮች በህልም አለም እንጂ በዕውን ሊያደርጉ የማይችሏቸውን ከሩዝ ውስጥ ድንጋይ መልቀም፣በመርፌ መስፋት፣ ከባባድ እንጨቶችን ለማንሳት የሚያገለግል ፑሊ መስራት፣ ቀስት በመስራት አርቆ መወርወር የመሳሰሉትን ክህሎቶቿን አሳየች፡፡ እግሮች ቁጭ ብለው የሸንቃጣዋ ዘመዳቸውን ድርጊት ከማድነቅ እና በሁኔታው ከመደመም ውጪ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡ እግሮችን በጣም ያበሳጫቸው ግን የተመልካቾች እጆች በህብረት በመሆን እጅን በማድነቅ ማጨብጨባቸው ነበር፡፡ ምንም እንኳን እግር እዝን ብሎ አሸዋ ላይ በወፍራም ጣቶቹ እየሳለ ቁጭ ቢልም፣ አሸናፊ የሚያደርገውን ውድድር እያሰበ ነበር፡፡
በመጨረሻም እግር የግጥሚያ ጥሪውን የሚያቀርብበት ሰዓት ደረሰ፡፡ እግርም ፈተናው በጣም ቀላል ነው እጆች የሚጠበቅባቸው ሙሉ ሰውነትን ተሸክመው መወዳደርያውን መዞር ብቻ ነው አለ፡፡ ግትሮቹ የእጅ ጣቶች ምን አይነት የማይረባ ጥያቄ ነው ብለው አሰቡ፡፡ ተገልብጦ ጉዞ የሚደንቅ እይታ ነበር፤እጆች መሬትን ረግጠዋል፣ አይኖች ለመሬት በጣም በመቅረባቸው የማየት አቅማቸው ተገድቧል፤ ወደ አፍንጫ አቧራ በመግባቱ እያስነጠሰ ይገኛል፤ እግሮችም አየር ላይ እየዋኙ ነው፡፡ ተመልካቹም ተዘቅዝቆ ጉዞ እግሮችን ይዞ እያሉ በደስታ አዜሙ፡፡
ተዘቅዝቆ ጉዞ እግሮችን ይዞ፣
ምን ጭንቅ አለ ውዴ ምን ሊያስፈራኝ ከቶ፣
ተዘቅዝቆ ጉዞ እግሮችን ይዞ፣
ምንም አያስፈራም እግርን ተከትሎ መብረር ነው በሰማይ፡፡
ሆኖም ትኩረታቸው በሙሉ ከጥቂት ደቂቃ በፊት የሚገርም ትርዒት ሲያሳዩ በነበሩት አሁን ግን ሰውነትን ተሸክሞ መንቀሳቀስ ያቃታቸው እጆች ላይ ነበር፡፡ ከጥቂት እርምጃዎች በኋላ እጆች ከህመም የተነሳ አነቡ ተንገዳገዱ፤በመጨረሻም ሰውነትን ገንድሰው ጣሉት፡፡ ከትንሽ እረፍት በኋላ ጣቶችን በመዘርጋት ሰውነትን ለመሸከም ያደረጉት ጥረት ከአውራ ጣቶች ውጪ ሌሎቹ ጣቶች መዘርጋት ባለመቻላቸው አልተሳካም፡፡ እግር እና እጅን ዘርግቶ በመሳብ ሰውነትን ለማንቀሳቀስ የተደረገው ጥረት እግርን ስላሳተፈ ውድቅ ተደረገ፡፡ እግሮች በተራቸው መሳቅ እና መደሰት ጀምረዋል፡፡ እጆች ካሽካኩበት ቀጭን ድምፅ ለመቃረን ወፍራም ድምፅ ከ አፍ ተውሰው መሳቅ ጀመሩ፡፡ የእግር ሽለላ ያበሳጫቸው እጆች በእልህ ሰውነትን ለመሸከም የመጨረሻ ሙከራ ቢያደርጉም እንድ እርምጃ እንኳን ለመራመድ እልቻሉም፡፡ ድክም ያላቸው እጆች በመጨረሻ እጅ ሰጡ፡፡ በጣም የተደሰቱት እግሮች ሰውነትን ሳይጥሉ በመንጎራደድ፣ በመሮጥ እና በመዝለል ችሎታቸውን አሳዩ፡፡ የታዳሚዎች እግሮችም መሬቱን በመርገጥ ደስታቸውን ገለፁ፡፡ ግጥሚያውን የጀመሩት እነርሱ መሆናቸውን የረሱት እጆች ተቃዉሟቸውን ከመግለፅ አላረፉም፡፡
ታዳሚዎችም ተወዳዳሪዎችም እጆች ሰውነትን ለመሸከም ጣቶችን ሲዘረጉ የተዘረጋው አውራ ጣት ከሌሎች ጣቶች ተለይቶ መቅረቱን አስተዋሉ፡፡ ተለይቶ መቅረቱ ሳያንስ የእጆች ሀይል መቀነሱ ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን በሳቅ ሊያፈነዳቸው ደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም የእጆች የመያዝ ችሎታቸውን ጨምሮላቸው ነበር፡፡ ይሄም በሁሉም ዘንድ የአካል ጉድለት የሃይል ምንጭ ይሆናል እንዴ የሚለውን ጥያቄ አጫረ፡፡
የግጥሚያውን አሸናፊ ለመለየት በሰውነት አካላት መካከል የተደረገው ክርክር በእጅ እና በእግሮች ላይ እንዳሉት ጣቶች አምስት ቀናትን ፈጀ፡፡ ምንም ያህል ቢሞክሩም በግልፅ አሸናፊውን ለመለየት አልቻሉም፡፡ ሁለቱም አካላት በየፊናቸው ግጥሚያቸውን ተወጥተዋል፤ አንዱም ከ አንዱ ተለይቶ ምንም ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ይሄኔም የተለያዩ መላምቶች ተነሱ፡፡ አካላት በሙሉ ሰውነት ምንድን ነው ብለው ጠየቁ ከዛም ሰውነት ማለት የእኛ ስብስብ ነው ተባባሉ፡፡ ሁሉም ተደጋግፈው መኖር አለባቸው አካላት በሙሉ ጤነኛ እንዲሆኑ አንዱ አካል ብቻውን ጤነኛ መሆን አለበት፡፡
ለወደፊቱ እንደዚህ አይነት ፉክክር እንዳይደገም አንዱም በአንዱ ላይ እንዳይነሳ ሰውነት በእግር ቆሞ እንዲራመድ እጅም እላይ አየር ላይ እንዲሆን የሰውነት አካላት ወሰኑ፡፡ ሰውነት በውሳኔው በጣም የተደሰተ ሲሆን ህፃናትን ግን አመጣጣቸውን እንዳይረሱ በአራት እግራቸው እንዲራመዱ ተወሰነ፡፡ የእጅ እና የእግር የስራ ድርሻም ተለየ፡፡ እግሮች ሰውነትን የመሸከም ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው፤ እግሮች ወደ መዳረሻ ካደረሱ በኋላም እጆች መያዝ የሚያስፈልጋቸውን መሳርያ ይዘው የሚሰሩትን ይሰራሉ፡፡ እግሮች ከባዱን የመሸከም ስራ ሲሰሩ እጆች ደግሞ ልዩ ክህሎታቸውን ተጠቅመው በአካባቢያቸው የሚሰራውን የመስራት እና ምግብ ወደ አፍ የማድረስ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ አፍ ወይንም ደግሞ ጥርስ ምግቡን አድቆ በጉሮሮ በኩል ወደ ሆድ የመላክ ሃላፊነት አለበት፡፡ ሆድም ምግብ ውስጥ ያለውን ጠቃሚ ነገር አጣርቶ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በቧንቧ በኩል የማስተላለፍ እና የማይጠቅመውን ወደ ውጪ በማስወገድ መሬትን የማለምለም ሃላፊነት አለበት፡፡ እፅዋት በለማው መሬት ላይ ያድጋሉ፤ እጆች ኮትኩተው አሳድገው ከፊሉን ይመገባሉ፣ አዎ ይህ ትክክለኛው የህይወት ዑደት ነው፡፡
ጨዋታ እና መዝናኛዎች ሳይቀሩ ለሰውነት ክፍሎች ተከፋፈሉ፡፡ መዘመር፣ማውራት እና መሳቅ ለአፍ ተተወላት፡፡ መሮጥ እና እግር ኳስ ለእግር፣ምንም እንኳን በእጅ ኳስ እና ቅረጫት ኳስ እግሮች የመሮጥ ሃላፊነት ቢኖርባቸውም ጨዋታው በዋነኝነት ለእጆች ሆነ፡፡ በአጠቃላይ ግን በአትሌቲክሱ ብዙ ሃላፊነት ያለው እግር ነው፡፡ የሰውነት ክፍሎች ስራ መከፋፈላቸው ሰው ከሌሎች ትላልቅ እንስሳቶች ይልቅ ውጤታማ እንዲሆን አደረገው፡፡
በመጨረሻ የተወሰነው የሰውነት አቋም አሁንም ግጭት ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከሁሉ በላይ የሚገኘው ጭንቅላት መሬት የሚረግጠውን እግርን እና ሌሎቹን የሰውነት አካላትን እንደ ባርያ እራሱን ደግሞ እንደ ጌታ ሊቆጥር ስለሚችል ነው፡፡ ስለዚህም በአቅም ጉዳይ ላይ ጭንቅላትም ሆነ ከስሩ ያሉት አካላት እኩል መሆናቸው አፅንዖት ተሰጠው፡፡ ይህንንም ለማፅናት አንዱ የሰውነት ክፍል የሚሰማው የትኛውም ስሜት ደስታም ይሁን ሀዘን ሁሉንም እንዲሰማቸው ሆነ፡፡ አንደበትም ይሄ ነገሬ ያ ነገሬ ብላ ስትናገር እንደ ብቸኛ ባለቤት ሳይሆን ሙሉ ሰውነትን ወክላ እንዲሆን አስጠነቀቋት፡፡ ከዛም የሚከተለውን አዜሙ፡-
የሰውነት ሀብቱ ነው መተጋገዙ፣
ባርያ የለ ጌታ ሁሉም አንድ ናቸው፣
ጤና ለመሆን ነው መተባበራቸው፤
በነሱ መሀከል የለም አዛዥ ታዛዥ፣
ይልቅ አንዱ ለአንዱ ነው ረዳትና አጋዥ፣
ይልቅ አንዱ ለአንዱ ነው ረዳትና አጋዥ፡
ቢሰሩ ቢለፉ እጅ እና ጓንት ሆነው፣
ለማንም አይደለም ጤና ለመሆን ነው፣
ለማንም አይደለም ጤና ለመሆን ነው፡፡
እኛ ለእኛ ብለን መተባበር ከቻልን፣
በአንድነት ውበት በአነድነት ሃይል፣
የትኛውንም ጠላት እናሸንፋለን፡፡
መዝሙሩ ሰውነት እስካሁን ድረስ የሚዘምረው ብሄራዊ መዝሙር ሆነው፡፡ በሰው እና ዘመቻ ቆሞ መሄድን ባልተቀበሉ እንስሳቶች መካከል ያለው ዋነኛ መለያቸውም ይህ ነው፡፡ ያዩትን ቢያዩም በአራት እግር የሚንቀሳቀሱት እንስሳቶች ዘመቻውን የመቀላቀል ፍላጎት አላደረባቸውም፡፡ መዘመር ምን አባቱ አፍ የተፈጠረው ለመብላት እንጂ ለመዘመር አይደለም ተባብለው ተፈጥሮን የመጠበቅ ድግስ ደግሰው አፈጣጠራቸውን ሳይቀይሩ ኑሮቸውን ቀጠሉ፡፡
ሰዎች ከአካላት ትብብር ሲማሩ መልካም ይሆናሉ፡፡ አካላትን ግን አንዱን የበላይ ሌላኛውን ደግሞ የበታች አድርገው ሲያስቡ ቆሞ የመሄድ ዘመቻውን ካልተቀላቀሉት ዘመዶቻቸው አይተናነሱም፡፡
~
Edited and read by Hewan Semon
Read the English translation – The Upright Revolution: Or Why Humans Walk Upright by Ngugi wa Thiong’o
Mahlet Lisanwork has a BA degree in English and another one in Public Administration from Addis Ababa University. She has done PR work for Orex International and Eminence Social Entrepreneurs. Currently, she is working for Ethiopian Airlines and does various kinds of translation works.
ማህሌት ልሳነወርቅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋዎች ጥናት የትምህርት ክፍል በእንግሊዘኛ ቋንቋ የመጀመርያ ዲግሪ እና በሌላ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ በህዝብ አስተዳደር የመጀመርያ ዲግሪ ያላት ሲሆን፤ በኦሬክስ ኢንተርናሽናል እና ኤምነንስ ሶሻል አንተርፕረነርስ ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ስራ ሰርታለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኛ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ እየሰራች በተጨማሪም የተለያዩ የትርጉም ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
You must be logged in to post a comment.