Now Reading
የአብይ ውሎ

የአብይ ውሎ

F-abiysday


Abiy’s Day” by Linda Yohannes Translated into Amharic by Mahlet Lisanwork

ሁለት ሰው በሚያስቀምጠው የታክሲ ወንበር ላይ ሶስተኛ ሰው ሆኖ ተደርቦ ወደ ስራው እየሄደ ሳለ ነው አብይ ዛሬ የሚያስተምረው በጥርሶች መሀከል ስለሚወጡ የእንግሊዘኛ ድምፀቶች እንደሚሆን የወሰነው፡፡ ሊዳሰሱ የሚገባቸውን አርዕስቶች ከዘረዘረ በኋላ በአምስት ደቂቃ ውስጥ የአዕምሮ ዝግጅት አደረገ፤በዚህም ለማስተማር ተዘጋጀ ማለት ነው፡፡ አዕምሮው ከዚህ ሀላፊነት ነፃ ከወጣ በኋላ ስለራሱ የሚሰማውን የታላቅነት ህይወት ወደ ማሰቡ ተመለሰ፡፡

በመሐል አዲስ አበባ ከተገነቡት አዳዲስ ህንፃዎች አንዱ ጋር ከታክሲው ወረደ እና ወደ ህንፃው አመራ፡፡ አሳንሰሩ ማንም ስላልነበረት ዘሎ በመግባት ወደ ዘጠነኛ ፎቅ አመራ፡፡ በአሳንሰሩ ውስጥ ባለው ረጅም መስታወት ቁመናውን ገመገመና ጥሩ አቋም ላይ ነኝ ያለሁት አለ፡፡ በአጭር ቁመናው ኮራ ብሎ መቆም አሳፍሮት አያውቅም፡፡ ጭንቅላት ከውጫዊ ውበት እንደሚበልጥ አሳምሮ ያውቅ ነበርና፡፡

ግራ የገባው ሁላ ረጅም መንገድ ሲጓዝ አብይ ግን ወደ ተሻለ ህይወት አቋራጭ ያገኘ ይመስል ይወጣጠር እና ነጠር ነጠር ይል ነበር፡፡

የተለመደው አይነት የአዲስ አበባ ቤተሰብ ውስጥ የተወለደው አብይ በጉዳዮቻቸው የተጠመዱ የቤተሰብ አባላት ውስጥ ነው ያደገው፡፡ በልጅነቱ በዲሽ የሚተላለፉ የካርቶን ፊልሞችን እያየ አደገ፡፡ ስለዚህም ጎርምሶ በራሱ ገላውን ለመታጠብ ሲበቃ ከቱፓክ ጋር ቃል በቃል ራፕ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ቆየት ብሎ ይህ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታው ገንዘብ ሊያገኝበት የሚችል መሆኑ ሲገባው በአዲስ አበባ በብዛት ከሚገኙት የቋንቋ ትምህርት ቤቶች በአንዱ አስተማሪ ሆነ፡፡

በክፍል ውስጥ ተማሪዎቹን በከፍተኛ የራስ መተማመን እጁን እያወናጨፈ ያስተምራል፤ምንም አይነት መፅሀፍ ወይም ወረቀቶችን በእጁ አይዝም፤ እንደዚህ አይነት በወረቀት እና በመፅሀፍ ላይ ያለ ጥገኝነት ለእንደሱ አይነቱ ምሁር አይሆንም፡፡

ምላሱን በጥርሶቹ መሀል እያሾለከ የእንግሊዘኛውን “th” ድምፅ በመፍጠር በጥርስ መሀል የሚፈጠሩ ድምፀቶችን አሳየ፡፡ “ምላሴን በጥርሶቼ መሀከል እንዴት እንደማወጣ እና በጠባቧ ክፍተትም አየር እንዴት እንደማስወጣ በጥንቃቄ ተመልከቱ፥ theatre, thin, thank! “Through” ሚባለውም እንደዚህ ነው እንጂ “ስሩ” አይባልም እሺ?” ክፍሉ አማርኛ ሲናገሩ ባደጉ ምላሳቸውን አንድ ቀን እንዲህ በል እንላለን ብለው አስበው በማያውቁ ወጣቶች የተሞላ ነበር፡፡ ለአብይ ግን ክብር ካስገኙለት ክህሎቶች ውስጥ አንዱ ይሄ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት እያለ አሜሪካዊው የእንግሊዘኛ ቅላፄው ለጥያቄ መልስ ከመለሰ በኋላ የክፍል ጓደኞቹ ለረጅም ሰዓት እንዲያፈጡበት ያደርግ ነበር፡፡ “Water”ን በሚርገበገብ “r” እንጂ ዋ-ተር አይልም፡፡ “Bau-ttle” እንጂ “ቦትል” አይልም ነበር፡፡ በክፍል ጓደኛቸው አፍ የሚሰሙትን ነጭ ሰው ለማየት አገጫቸውን ወደ ላይ ቀስረው ያዩታል፡፡ በ15 አመት የክፍል ጓደኞቹ አይን እንግሊዘኛን አስመልክቶ ሁሉን ቻይ ተደርጎ መታየቱን ለተፈጠረበት ለእያንዳንዱ ጉዳይ እንደሚሰራ ያስብ ጀመረ፡፡

ጥርስ እና ምላሱን አፍጥጠው የሚመለከቱት ተማሪዎች ላይ እጁን እያወናጨፈ “እሺ! እስቲ በድጋሚ “th-rough” በሉ አላቸው”፡፡

አብይ በዚህ ትምህርት ቤት ባስተማረባቸው ሁለት አመታት ደስተኛ ነበረ፡፡ ሆኖም ከዚህ የበለጠ ደስታን ይፈልግ ነበር፡፡ ትልቁ ስኬቱ ይጀምር ዘንድ ተመኘ፤ እንዲሁም በውስጡ ወደ ሚሰማው ነገር ያ በመስታወት እራሱን ሲያይ ከቆዳው ስር ሲምቦጎቦግ ወደሚያየው ነገር መጠጋትም ፈለገ፡፡ በአንድ ባር ከጓደኞቹ ጋር ቁጭ እንዳለ ሲጋራውን በእጁ እንደያዘ ሀብታም እንደሚሆን አስረግጦ ነገራቸው – አንድ ሰው ሀብታም ስለመሆን ያለውን ምኞትና እቅድ ለራሱ መያዝ ያለፈበት አስተሳሰብ ነው ብሎ ያስብ ነበር፡፡ የዩንቨርሲቲ ተማሪ እያለ እንዴት መበልፀግ እንደሚቻል በሚያወሩ እና ሚሊየነር መሆንን የወረቀት ጀልባ የመስራት ያህል በሚያቀሉ መፅሀፍቶች ፍቅር ተነድፎ ነበር በጣምም ያምናቸው ነበር፡፡

አብይ የአውራ ጣቱን ጥፍር እየበላ ብዙ ብር የሚያስከፍሉ ስራዎችን እንዴት ማግኘት እንደሚችል ያስብ ገባ፡፡ አንዴ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ምሁራን ዘንድ ከታወቀ፤ ባለሀብቶቹን በተራ ማሳመን እና መቀጠር እንደሚችል ያውቀዋል፡፡ ከዛም በአንድ ትልቅ በሆነ አሁን በግልፅ ባላወቀው እርምጃ ከሁሉም የበላይ ሆኖ ሌሎችን ቀጥሮ ሲያሰራ ታየው፡፡

ጋዜጣ እያገላበጠ ክፍት የስራ እድሎችን ሲያፈላልግ በአገሪቱ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ምርጥ አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች አንዱ ያወጣውን ማስታወቅያ አከበበበት፡፡ ትምህርት ቤቱ የአፍሪካ ዲፖሎማቶች እና በከተማው የታወቁ ነጋዴዎች ልጆች የሚማሩበት ነው፡፡ ለዚህ ስራ ማመልከት እንዳለበት ወስኖ የማመልከቻ ናሙናዎችን ለማግኘት ኢንተርኔት መጎርጎር ጀመረ፡፡ ከዛም “የመጀመርያ ዲግሪዬን በእንግሊዘኛ ትምህርት የማዕረግ ተመራቂ ስሆን እንግሊዘኛን ጥርት አድርጌ እናገራለው” ብሎ በከፍተኛ የራስ መተማመን ፃፈ፡፡

ሳምንቱን ሙሉ ስልኩ ላይ ሲያፈጥ ሚስ ኮሎችንም ያለድካም ሲመልስ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ምንም እንኳን ብዙ ባይደንቀውም ለቃለ መጠየቅ ተጠራ፡፡

አብይ ያን ያህል ባይሆንም ለቃለ መጠይቁ ተዘጋጀ፡፡ ቃለ መጠይቁ ነገ ሊሆን ማታ ላይ ተከራይቶ በሚኖርባት አራት በ አራት የሆነች አንድ ክፍል ቤት ውስጥ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደታች እየሄደ ይጠየቃሉ ብሎ ላሰባቸው ጥያቄዎች መልሶችን ተለማመደ፡፡

ፍተሻ ላይ መታወቂያውን ካሳየ በኋላ፣ ከመግቢያው በር እስከ አስተዳደር ቢሮ ያለውን ረጅም ርቀት በአለም ሙቀት መጨመር የተነሳ በአዲስ አበባ በሚታየው ቆዳን በሚበሳው ፀሀይ እየተቃጠለ ሄደ፡፡ ለፕሮግራሙ የሚመጥን አለባበስ ለመልበስ ሞክፘል፡፡ የሚያብረቀርቅ ቆዳ ጫማ፣ ግራጫ ሱሪ፣እንዲሁም ለአለባበሱ ማድመቂያ ቦርሳ በእጁ ይዟል፡፡ ወደ ውስጥ ሲገባ አፍንጫውን በጣቱ ጠረግ ሲያደርግ ጣቱ ቅባታማ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ አዎ ትክክለኛው ቦታ ላይ ነው ያለው ሰዎች በቡድን በቡድን ሆነው ቆመዋል ብዙዎቹ ደግሞ በዕድሜ ከእርሱ ጠና ያሉ ናቸው፡፡ አለባበሳቸው የድሮ ስታይል ሆነበት፡፡ ወንዶቹ ቦርጫቸው በጥቁር እና ቡኒ ቀበቶዎች አስረዋል፡፡ የሴቶቹንም የፀጉር ስታይላቸውን አየና ስራው የእርሱ እንደሆነ አመነ፡፡ ትላልቆቹ ሰዎች አየት አረጉት፡፡ እርሱም ትላልቆቹን ሰዎች እያየ ለራሱ እንደዚህ አለ እነሱ የሚፈልጉት እንደናንተ አይነት ሰው አይደለም አይተውኝ ብቻ የሚፈልጉት ሰው እኔ እንደሆኑኩ ያውቃሉ፡፡

የሚፈልጉት ሰው እርሱ መሆን አለበት ምክንያቱም ከእርሱ ውጪ የሆነ ሰው እሱ የተለየ ሰው መሆኑን ሚያውቅበት ወሳኝ ጊዜ ህልሙም እውን የሚሆንበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ በመጨረሻ ለቃለ መጠይቁ ተራው ደረሰ እና ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ኮርኒስ ድረስ የሆነ ሙሉውን መፅሃፍት የተደረደረበት ሼልፍ ፊትለፊት ዝም ብለው ቁጭ ያሉትን ሁለት ሰዎች ሲያይ ከፍተኛ የነበረው የራስ መተማመኑ ተነነ እና የቀረችውን ለመጠበቅ እራሱን መጠባበቁን ተያያዘው፡፡ ሁለት የሚያምር አለባበስ የለበሱ ወንድ እና ሴት ነጮችን አየ፡፡ እግራቸው ላይ ወረቀቶችን እና በእጆቻቸው ደግሞ እስኪብሪቶ ይዘዋል፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ከአገሩ ህዝብ ጋር እንደማይወዳደር ይሰማው ነበር ከተወላጆቹ ማለትም ከዋና እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ጋር ግን ሌላ ታሪክ ነው፡፡

ባልተቀናጀ ሁኔታ “ለቃለ መጠይቅ ነው የመጣሁት” ለማለት ”r”ን ደጋገማት፡፡ ነው ወይስ ትንሽ አዳለጠው? አንዳንዴ ቅላፄው የተቀቀለ ቲማቲም ልጣጭ ይመስል በአፉ ጎን እና ጎን ፍትልክ እያለ ያመልጠዋል፡፡ ሆኖም ጠያቂዎቹ ያወቁበትም የተማረኩበትም አይመስሉም፡፡

ሴትየዋም እስኪብሪቶ የያዘውን እጇን እያወዛወዘች “በትክክል እባክህን ግባ” አለችው ከተቀመጠ በኋላም “ሰላም” አለችው በአማርኛ እንደ ጓደኛ ለመቅረብ እየሞከረች፡፡ ለሚቀጥሉት አስር ደቂቃዎች አብይ ስለራሱ እና ስለማስተማር ልምዱ ባወራ ቁጥር ጠያቂዎቹ የሚለውን ማሰብ የማይፈልጉ ሁኔታ በጣም ያዩት ነበር፡፡

በማስከተል “የጀማሪዎች ኮርስ ለጀማሪ ተማሪዎች ብዙ ጊዜ ሰጥቻለው” ለማለት ኢንትሮዳክተሪን ኢንሮዳተሪ “in-rodu- tory” ብሎ ቀለፃት፡፡

ያነባበረችውን እግፘን እያወረደች ወደፊት ጠጋ በማለት ጆሮዋን በደንብ ሰጥታ “ይቅርታ ምንድነው ያልከው? በድጋሚ ትልልኛለህ?” አለች ሴትየዋ፡፡ የአውራ ጣት ጥፍሩን እየቆፈረ እንድትረዳው እንደተማሪዎቹ መቀለፅ ግዴታው ሆነ፡፡

“እ! የጀማሪዎች ኮርስ (Introductory courses) እሺ፣ ጥሩ”
እንግሊዘኛ ቋንቋን እንደ ሁለተኛ ቋንቋ የማስተማር ሳይንስን በተመለከተ ጥያቄዎችን ጠይቃ አስጨነቀችው፡፡ አብይ ሰውየው የሆነ ነገር ቢል እና ቢገላግለው ተመኘ፡፡

ፊት ለፊት እያየችው “ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን እንግሊዘኛ ስለማስተማር ያሉ ዋና ዋና የሆኑት ነገሮች ምንድናቸው ትላለህ?” አለችው፡፡

እያጉረመረመ ምርጥ የሆነው ምላሽ ምን እንደሆነ ያወጣና ያወረድ ጀመር፡፡ “ለምሳሌ ሰዎች ያደጉበት የመጀመርያ ቋንቋቸው ድምፀት እና ቅላፄ እንግሊዘኛን እንደ ተወላጆቹ ለመቀለፅ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል” አለች ሴትየዋ ቀጠል በማድረግም “ይሄም አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎችን ቋንቋውን እንዳይለማመዱ ያደርጋቸዋል” አለች፡፡

አብይ ማድረግ የሚችለው ነገር በግንባሩ መስማማቱን ማሳየት ብቻ ነበር፡፡

ፈገግ እያለች “ለዚህ ነው ሌሎች የሚረዱትን ነገር መናገር ከቅላፄ ይበልጣል ብለን ምናምነው፡፡” አለችው፡፡

ወደ ውጪ ሲወጣ እነዛ ትላልቆቹ ተወዳዳሪዎች ለቦታው በውስጥ ማስታወቂያ ያመለከቱ የመስራቤቱ ቅጥረኞች መሆናቸውን በደረታቸው ላይ ባንጠለጠሉት መታወቂያ አወቀ፡፡

ከህንፃው እሮጦ ወጣ አሁን ደግሞ እየዘነበ ነው፡፡ በአዲስ አበባ አሁን ፀሀይ ነው ሲባል ወዲያው ደግሞ ዝናብ ይሆናል፡፡ እሱ ደግሞ ጥሎበት የጥላ ግዢን ሁሌ ለነገ እንዳለ ነው፡፡ ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ወጥቶ እየባሰበት የመጣውን ዝናብ ለማምለጥ የሚፘፘጠውን ህዝብ ተቀላቀለ፡፡ ይሄኔም ዕጢው ዱብ ሲል ተሰማው፡፡

ዝናቡ የጫማው ቀለም ላይ እየተንሸራተተ በዝናቡ ውስጥ መሄዱን ቀጠለ፡፡


Mahlet Lisanwork has a BA degree in English and another one in Public Administration from Addis Ababa University. She has done PR work for Orex International and Eminence Social Entrepreneurs. Currently, she is working for Ethiopian Airlines and does various kinds of translation works.

ማህሌት ልሳነወርቅ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋዎች ጥናት የትምህርት ክፍል በእንግሊዘኛ ቋንቋ የመጀመርያ ዲግሪ እና በሌላ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ በህዝብ አስተዳደር የመጀመርያ ዲግሪ ያላት ሲሆን፤ በኦሬክስ ኢንተርናሽናል እና ኤምነንስ ሶሻል አንተርፕረነርስ ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ስራ ሰርታለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የደንበኛ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ እየሰራች በተጨማሪም የተለያዩ የትርጉም ስራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡

Linda Yohannes (@LindaYohannes) is an Ethiopian writer. Since in secondary school, she has written for and edited several publications. She has an MA in English Literature from Addis Ababa University where she taught English and Literature courses for four years. In 2012, she won the Burt Award for African Literature and her short novel for young readers titled The School Newspaper was published. She is manager and writer at The Writing Company, her own enterprise, and is currently working on short stories and a novel.

What's Your Reaction?
Excited
0
Happy
0
In Love
0
Not Sure
0
Silly
0
Scroll To Top